MAHEDER HAILESELASSIE

በወሸባ ወቅት መነበብ የሚገባቸው አምስት ጥሩ የግለሰብ ታሪኮች

(በቪዲዮ ለማየት ከፈለጉ ይኽንን መስፈንጠሪያ ይጫኑ።)

የግል ታሪኮችን እንደማንበብ የሚያስደስተኝ የለም ነገር ግን በስራ ተወጥሬ ሰነፍኩና በዚኽ አስቸጋሪ ወቅት ስራ ጋብ ሲል እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝቼ ካስቀመጥኳቸው መጻሕፍት መሀከል የተወሰኑትን ለማንበብ ወሰንኩ። ለመምረጥ ቢቸግርም በትክክል መነበብ ይገባቸዋል ያልኳቸውን ከዚኽም ከዚያም አድርጌ ከጠቀማችኹ እንድትመርቁኝ እነሆ:- 

1. ‘ማስታወሻ’ - ዘነበ ወላ 

ጋሽ ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር ላይ ያልደረሰ እና በዝና ብቻ ለሚያውቃቸው፣ ማስታወሻ እርሳቸውን ብቻ ሳይኾን የርሳቸውን ጊዜ ትውልድ፣ የሕይወት ፍልስፍናቸውን እና ጣፋጭ ገጠመኞቻቸውን እያዋዛ ከርባገረድ፣ ትግራይ  እስከ ዐዲስ አበባ፣ከውቤ በረሀ እሰከ ጃንሆይ ደጃፍ፣ከኒውዮርክ እስከ ፓሪስ ድረስ ያስኮመኩማችኋል። 

መጽሐፉ መግቢያ ላይ ጋሽ ስብሐት ለአብ እንዲህ ጽፏል።

‘የዘነበ አጋሮች (ጋሞ የሚባሉት) አብሯቸው የሌለውን፣የሚያከብሩትን፣የሚያደንቁትን ሰው ሲያስታውሱት ‘ኢዚ ባይንታ ሶን ኢዛ ሱንሳ ዴንሳሼ ሀኢካ ኢዛስ ኤቃይስ!’ ይላሉ። ‘እሱ በሌለበት ስሙን ሳነሳው ፣ ተነስቼ ቆሜ ‘ኖር’ እያልኩት ነው’ እንደማለት ነው።’

መጽሐፉን ስትጨርሱ ለጋሽ ስብሐት ለአብ እና እርሱን ሳይሰስት ላቋደሰን ለጋሽ ዘነበ ወላ ኖር እያላችኹ እጅ እንድትነሱ ትገደዳላችኹ።

(የጋሽ ስብሐትን ማንነት ለመገንዘብ በዚኽ ቪዲዮ ላይ ለሚታዩት ሽንፍላ የሚልጡ ጥያቄዎች የሚሰጡትን መልስ ማየት አንድ ጅማሬ ነው።)

2.  ‘የሕይወቴ ታሪክ’ - ፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት ተክለ ማሪያም


እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ1880ዎቹ መጀመሪያ የተወለዱት ፊታውራሪ ተክለሐዋሪያት ለቤተ መንግሥቱ ከነበራቸው የተገራ ቅርበት አንጻር ከርሳቸው የተሻለ ወቅቱን የሚያስገነዝብ አጉሊ መነፅር ማግኘት ይከብዳል። በተለይ በልጅ ኢያሱና በደጃዝማች ተፈሪ መሀከል የነበረውን የስልጣን ሽኩቻ በኋላም ተፈሪ ከነገሱ በኋላ ሀገራችን የተጓዘችበትን ቀና እና ጎርባጣ መንገዶች ሁሉ በጠንካራ የፍትሕ ሚዛን ላይ አስቀምጠው ይመዝናሉ።  ፊታውራሪን የሚያሳይ የ1፡13 ደቂቃ ቪዲዮ ይኸው

3. ‘በዓሉ ግርማ -ሕይወቱና ሥራዎቹ’ - እንዳለጌታ ከበደ

የእንዳለጌታ ከበደን የመጻፍ ጉልበት ያላመነ ሰው በ’በዓሉ ግርማ፦ ሕይወቱና ስራዎቹ’ ይረታል። በዓሉን ከስም አጠራሩ ጀምሮ እስከ እንቆቅልሽ አሟሟቱ ድረስ አዛውንቶችን እየጠየቀ እና ከራሱ ከበዓሉ ጽሑፎች ሳይቀር እየመዘዘ ያለውን አቅም ኹሉ አሟጦ ከዚኽ በፊት ፀሐይ ያልሞቃቸውን ድንቅ ታሪኮች በራሱ እና በሰው አፍ ያወጋናል። በዓሉን ያወቅሁትም፣የወደድኩትም፣ከልቤ ያዘንኩለትም በዚኽ መጽሐፍ ነው ማለት እችላለኹ - ዕድሜ እና ሙሉ ጤና ለእንዳለጌታ ከበደ።

በዓሉ ግርማ ስለ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አገልግሎት የሚናገርበትን ቪዲዮ እነሆ 

4. ‘ማማ በሰማይ ላይ’ - ሕይወት ተፈራ 

ሕይወት ተፈራ “Tower in the sky” ወይም ማማ በሰማይ ላይ ብሎ በተተረጎመ ጥሩ መጽሐፏ  ያን ትውልድ የሚወቅሱ እና የሚከሱትን ኹሉ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ የዚያን ትውልድ የአላማ ጽናት እንዲቀበሉና እንዲያደንቁ ያስገደደች ይመስለኛል።  ከኅቡዕ ድርጅት አባልነት ጀምሮ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ የርሷን እና የትግል አጋሮቿን ጉዞ ትተርክልናለች። 

ጸሐፊዋ ራሷ ለመዓዛ ብሩ በአንድ ወቅት በሰጠችው ቃለ ምልልስ መጽሐፉ ሳይታተም በፊት የጌታቸው ማሩን ኮት ከመቃብር በላይ ተሰቅሎ በህልም እንዳየች ነግራናለች። እውነትም ፍቅራቸው እና ፅናታቸው ልባችን ውስጥ ታትሞ እስኪቀር ድረስ ስሙን ከመቃብር በላይ አውላዋለች። ሳይሰለች የሚነበብ መጽሐፍ ነው።

5. ‘Makes me wanna holler’ - Natan McCall 

ከታተመ ኻያ ዓመታት ቢያልፉትም ናታን ማክኮል ከጥቁር አሜሪካውያን አሳዛኝ የዘረኝነት ጥቃት እስከ እስርቤት እና ታዋቂ ጋዜጠኝነት ድረስ ያለፈበትን እያንዳንዷን ርምጃ ለአንባቢ ራሱ በሚዘገንን ግልፅነት እና ሀቀኝነት  ይተርክልናል። ሕይወትን ከናታን ታሪክ በላይ አስቸጋሪ አድርጎ መሳል ይከብዳል።  

ደግ ሰው እስኪተረጉምልን ድረስ ከአማዞን ላይ መግዛት ከቻሉ ሊንኩ ይኸው። 

ጭማሪ፦ በአዲስ አበባ ገበያ ላይ ከምታገኟቸው እንግሊዘኛ መጻሕፍት መሀከል የኬቨን ሀርት “I can’t make this up’ እና የትሬቨር ኖሀ ‘Born a crime’ የምወዳቸው ናቸው። የኋለኛውን ጥላሁን የተባለ ወጣት ‘የአበሳ ልጅ’ ብሎ በግሩም ተርጉሞታል ተብሎ ሰምቻለኹ። አማርኛዎቹ ድንቅ ግለ-ታሪኮች መቼም በአራት ብቻ የሚደመደሙ ስላልኾነ የሥዩም ወልዴ ራምሴን ‘ኩርፊያ የሸፈነው ፈግግታ’ ጨምሬ ለአኹኑ ብቻ በዚኽ ላብቃ።


Using Format